29/12/2025
ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ ጥቅሎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን በይፋ አስታወቀ‼️
እየታዩ ያሉትን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመሩ ያሉ የካፒታልና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መጠነኛ የታሪፍ ማስተካከያ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህ ማስተካከያ ኩባንያችን ለደንበኞቹ የሚሰጠውን ሰፊ አገልግሎት ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና በመላ አገሪቱ እያካሄድን ያለውን የቴሌኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል መሠረተ ልማት መስፋፋትን በዘላቂነት ለማጠናከር እና ወደፊት ለማራመድ ነው።
ይህ ማስተካከያ ሲደረግ የደንበኞቻችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከተሉት ነጥቦች ታሳቢ ተደርገዋል፦
የቴሌብር ልዩ ስጦታ፦ በቴሌብር ጥቅል ሲገዙ የነበረው የ10% ቅናሽ ወደ 20% ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ዋጋቸው ያልተቀየሩ ጥቅሎች፦ በርካታ ደንበኞች የሚጠቀሙባቸው 38 የተለያዩ ጥቅሎች ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደረገም።
ዲጂታል አካታችነትን ለማስቀጠል፦ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙባቸው የ1 ብር፣ የ2 ብር፣ የ5 ብር እና የ1 ሰዓት ጥቅሎች ባሉበት ቀጥለዋል።
ልዩ ጥቅል፦ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለተማሪዎች እና ለመምህራን የተዘጋጁ ልዩ ጥቅሎች ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አልተደረገም።
ለዘወትር አብሮነታችሁ እያመሰገንን፣ የዜጎችን ኑሮ የሚያዘምኑ የዲጂታል መፍትሔዎችን ማቅረባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን!